የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት በዓል ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ተከበረ

የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ የተጣለበት 13ኛ ዓመት በዓል ‘በህብረት ችለናል’ በሚል መሪ ቃል ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ ተከበረ። በበዓሉ ላይ የሀይማኖት አባቶች፣ ምሁራን፣ የተለያዩ አደረጃጀት አመራሮች እንዲሁም ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት ለህዳሴ ግድቡ አስተዋጽኦ ያደረጉ እና አዳዲስ የዳያስፖራ አባላት የተሳተፉ ሲሆን በኤምባሲው በአካል ከተገኙት በተጨማሪ በርካታ ተሳታፊዎች በበይነ መረብ ተገኝተው ዝግጅቱን ተከታትለዋል።

በበዓሉ ላይ በአሜሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ባስተላለፉት መልዕክት የህዳሴ ግድባችን ሁሉም ዜጋ ሀብቱን፣ ዕወቀቱን፣ ጊዜውን በማስተባበር የሚገነባ ልዩ ፕሮጀክት መሆኑን እና ግንባታው አገራችን በልማት እጦት ካለችበት የኋላ ቀር ኢኮኖሚ ለመውጣት፣ ለህዝቦቿ የሚያስፈልገውን የኢነርጂ መሰረት በመገንባት ዕድገት፣ ብልጽግና እንዲሁም አገራዊ ሀብት መፍጠር የሚያስችለን ወሳኝ ተግባር ነው ብለዋል። በተጨማሪም ይህንን ፕሮጀክት ከጅምሩ አንስቶ እስካሁን ድረስ ይመለከተናል በማለት ገንዘባቸውን፣ እውቀታቸውን እና ጊዜያቸውን ሳይሰስቱ የበኩላቸውን ድርሻ ለተወጡ የዳያስፖራ አባላት ያላቸውን ከፍተኛ አክብሮት እና ምስጋና የገለጹ ሲሆን፣ ግድቡ እስኪጠናቀቅም ይኸው ተሳትፎ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

ከተሳታፊዎች በቀረቡ አስተያየቶችም ለህዳሴ ግድቡ የሚደረጉ ድጋፎች ከየትኛውም የፖለቲካ አመለካከትና ውግንና ነጻ የሆነ እና ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ የሚረባረብበት መሆኑ እና ከዚህ ቀደም እንደሚያደርጉት ሁሉ ግድባችን እስኪጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ቃል ገብተዋል። በዕለቱም ለታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሂዷል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *