128ኛዉ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል
128ኛዉ የአድዋ ድል መታሰቢያ በዓል ”አድዋ የጥቁር ህዝቦች ድል” በሚል መሪ ቃል በአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለ ሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በተገኙበት የካቲት 23/2016 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ በድምቀት ተከብሯል።
ክቡር አምባሳደር ዶ/ ር ስለሺ በቀለ በአሉን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት የአድዋ ድል የአንድነት እና የትብብር ፅናት የታየበት የመላው ኢትዮጵያውያን ድል ሲሆን፣ ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካና ለመላው ዓለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ጎህን የቀደደ እንደሆነ በማውሳት የእምቢ አልገዛም ባይነት መንፈስን ለመላው ጭቁን ህዝቦች ያጎናጸፈ ወደር የለሽ የነፃነት ተጋድሎ ምልክት መሆኑን አውስተዋል።
በመቀጠልም በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከአደዋ ድል በመማር እና ልምድ በመቅሰም በትዉልድ በሀገራቸው አስተማማኝ እና ዘላቂ ሰላም፣ እድገት እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ እየተደረጉ ባሉ ጥረቶች ዉስጥ የራሳቸውን አሻራ በቁርጠኝነት ማሳረፍ እንደሚገባቸዉም ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም በአል ላይ በርካታ ታዳሚዎች የተገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የእምነት አባቶች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች፣ አትሌቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣ የዳያስፖራ አደረጃጀቶች አመራሮች እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው::
በዓሉንም ለመዘከር የተለያዩ ታዋቂ ግለሰቦች እና የኢትዮጵያ ወዳጆች መልእክቶችን አስተላልፈዋል:: እንዲሁም የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች እና የአድዋ ጀግኖች ገድለ ታሪክን የሚያሳይ ጽሁፍ እና ቪዲዮ እንዲቀርብ ተደርጎዋል::
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!