በዲ.ኤም.ቪና አካባቢዉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ማሰሪያ የመጨረሻ ዙር የነፃ ልገሳ የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸዉ ተገለጸ፤

እ.ኤ.አ ጁን 19/2025 በዲ.ኤም.ቪ እና አካባቢዉ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በተገኙበት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡

በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ሁነት ላይ በዋሽንግተን ዲሲ፣ በሜሪላንድና በቨርጂኒያ (DMV) የሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የግል ባላሃብቶች፣ አደረጃጀቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት አመራሮች፣ ታዋቂና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች በተለይ ደግሞ ከዚህ ቀደም ለግድቡ ግንባታ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያከናውኑ የቆዩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የነቃ ተሳትፎ የታየበት ሲሆን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱዓለም ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የህዳሴ ግድብ መላው ኢትዮጵያውያንን በአንድንት ያስተሳሰረ የኩራታችን መገለጫ ነዉ ብለዋል። ይህ እንዳለ ሆኖ ከበርካታ ዉጣ ዉረዶች በኋላ መንግስት በወሰዳቸዉ ቆራጥ ስትራቴጂያዊ እርምጃዎች በተገኘ ዉጤት በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ዋዜማ ላይ በመናኘታችን እንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጨረሻ ምዕራፍ ከ 2 ፐርሰንት ያነሰ ስራዎች ብቻ የቀሩት መሆኑንና ይህንንም ለማጠናቀቅ እንዲቻል እንደ ከዚህ ቀደሙ አሻራችንን ለማስቀመጥ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ዲያስፖራው ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል። በመቀጠልም ዳያስፖራዉ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ላበረከተዉ የበኩሉን ድርሻ እና እስካሁን ላደረገዉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የዕዉቅና እና የምስጋና ሰርተፊኬት በኤምባሲዉ ተበርክቶላቸዋል፡፡

በዕለቱም ለግድቡ ማጠናቀቂያ የመጨረሻ ዙር ገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይ አንድ መቶ ሃያ ሁለት ሺህ (122,000) የአሜሪካ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንዲሁም ሰላሳ አራት ሺህ ስምንት መቶ ሁለት (34,802.00) የአሜሪካን ዶላር ቦንድ ከሃገር ቤት ለመግዛት ቃል የተገባ ሲሆን በዚህ ዓመት እስከ አሁን ድረስ ከዩናትድ ስቴትስ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በድምሩ ሁለት መቶ ሰላሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ሰባ አራት (231,174) የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዚህ ፕሮግራም ላይ አንድ ሀገር ወዳድ ታዋቂ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የግል ባለሃብት ከ2021-2024 ባሉት ጊዜያት ዉስጥ ብቻ ከአንድ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጄክት ማሰሪያ የነጻ የገንዘብ ድጋፍ ማበርከታቸዉ ለመላዉ ኢትዮጵያዊያን ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑ ተነስቶ ለዚህም ታላቅ ምስጋና እና ዕዉቅና ተሰጥቷል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *