ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ በጽ/ቤታቸዉ ተቀብለዉ አወያይተዋል

እ.ኤ.አ ማርች 14/2024 በአሜሪካ የኢፌዴሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዶ/ር ስለሺ በቀለ በሰሜን ካሊፎርኒያ እና አካባቢዉ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል በሆኑት በብጹዕ አቡነ ቴዎፍሎስ የሚመራ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ኅብረት የልዑካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸዉ ተቀብለዉ አወያይተዋል።

በዉይይቱ መክፈቻ የቡራኬ ፀሎት ከተካሄደ በኋላ ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል። በመቀጠልም የዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የስራ እንቅስቃሴን አስመልክቶ አጭር ገለጻ ያደረጉ ሲሆን ከዚህ ሌላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ-ስብከት ሀገራዊ ጥሪን ተቀብሎ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ለኮቪድ 19 መከላከል፣ በተፈጥሮ እና በሰዉ ሰራሽ አደጋ ለደረሰ ጉዳት ማለትም በተለያዩ ክልሎች በተለይ ደግሞ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተካሄደዉ ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ፣ ለመሰረተ ልማት ግንባታ እና ለተለያዩ የልማት ስራዎች ከፍተኛ ድጋፍ በማድረግ የሀገር አለኝታነትዋን እንዳረጋገጠች በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል። ክቡራን ብፁአን ሊቃነ-ጳጳሳትና የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች ቀደም ብለዉ በደብዳቤ የላኳቸውን ጥያቄዎቻቸዉ አቅርበዉ ዉይይት እንዲደረግ ጋብዘዋቸዋል።

በዚህ መሰረት በ27/06/2016 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ህብረት ለሚሲዮኑ የተፃፈ ባለ ስድስት ነጥቦች ጥያቄዎችን ለመንግስት በማቅረብ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል። ህብረቱ ካነሳቸዉ ጥያቄዎች መካከል ዋና ዋናዎቹን ለመጥቀስ የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ፀሃፊ እና የኒዉዮርክ እና አካባቢዉ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ የብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ በሲኖዶሱ ፈቃድ ለሃይማኖታዊ ተልዕኮ ወደ ኒዉዮርክ ሄደዉ ሲመለሱ ወደ ሀገር ቤት እንዳይገቡ የመከልከላቸዉ ምክንያት ግልጽ ያለመሆን እና መንግስት ይህን ያደረገበትን ምክንያት እንዲገለጽላቸዉ ጠይቀዋል። ድርጊቱ ቅድስት ቤተክርስቲያኒቷን የማይመጥን፣ ሉዓላዊ ክብሯን የሚጋፋ እንደሆነ በማንሳት በአግባቡ ታይቶና ተጣርቶ አስፈላጊዉ የእርምት እርምጃ በአፋጣኝ እንዲወሰድ፣ ከዚህ በተጨማሪ ከሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት በኤምባሲ እና በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ ዕዉቅና አግኝቶ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት አገልግሎት ለማስጀመር እንዲቻል፣ በእርዳታ የተላኩ በርካታ የቴክኖሎጂ ዕቃዎች ያላንዳች በቂ ምክንያት ከቦሌ አየር ማረፊያ እንዳይወጡ መደረጉ ተገቢ እንዳልሆነ፣ በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም መነኮሳት ላይ በግፍ የተፈፀመዉ አሰቃቂ ግድያ ምክንያቱ ምን እንደሆነ፣ የድርጊቱ ተጠያቂ ማን እንደ ሆነ፣ የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎች ተነስተዉ የነበረ ሲሆን በእነዚህ እና በሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ዉይይት ተካሄዷል።

በመጨረሻም ክቡር አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሰሜን አሜሪካ አህጉረ ስብከት ኅብረት ለኤምባሲያችን የተላከዉ ደብዳቤ ምላሽ ያገኝ ዘንድ ለኢፌዴሪ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚልኩ እና ቀጣይ ክትትል እንደሚያደርጉ በማንሳት በሚስዮን ደረጃ መመለስ ያለባቸዉ ጉዳዮችን ደግሞ በመለየት ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚሰሩ ገልፀዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እጅግ በርካታ ቁጥር ያለዉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ምዕምናን ያላት እንደ መሆኑ መጠን እንደ ካሁን ቀደም ሁሉ ዳያስፖራዉ በኢትዮጵያ ልማትን እና ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገዉ ሁሉ አቀፍ ጥረት በመሳተፍ አሻራዉን እንዲያሳርፍ የበኩሏን ሚና እንድትጫወት ጥሪ አስተላልፈዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *