የኢትዮጵያን እምቅ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ እሴቶች ለአሜሪካዊያን ጎብኝዎች የሚያስተዋውቅ ዝግጅት

መጋቢት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኤምባሲ የኢትዮጵያን እምቅ ታሪካዊ፣ ባህላዊ እና ተፈጥሯዊ እሴቶች ለአሜሪካዊያን ጎብኝዎች የሚያስተዋውቅ ዝግጅት በርካታ ተሳታፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፣
የዝግጅቱ ዋና ዓላማ አገራችን ኢትዮጵያ በቱሪዝም መስክ ያላትን መስህብ ለአሜሪካዊያን ለማስተዋወቅና አገራችንን እንዲጎበኙ ግንዛቤ ለመፍጠር ያለመ ሲሆን፣ ’Things to do DC’ የተሰኘ ተቋም ዋሽንግተን ዲሲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ መድረክ ነው።
በዝግጅቱ ላይ የኤምባሲው ምክትል ሚሲዮን መሪ አምባሳደር ዘላለም ብርሃን ባስተላለፉት መልዕክት ኢትየጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የጥንት ስልጣኔ ባለቤት፣ የራሷ ፊደልና ዘመን አቆጣጠር ያላት፣ ቡናን ለዓለም ያበረከተች፣ በዩኔስኮ የተመዘገቡ 13 ያህል ቅርሶች ባለቤት፣ በአፋር የሚገኘው አስደናቂ የእሳተ ገሞራ፣ የበርካታ ባህሎች ስብጥር፣ የኮንሶ የባህላዊ ገጽታ፣ በርካታ የአጥቢ እንስሳትና አእዋፍ ሀብት የሚገኙባት እና የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት የሆነው አድዋ ድል ባለቤት መሆኗን አስታውሰዋል።

አምባሳደሩ አክለውም ኢትዮጵያ በአፍሪካ እጅግ ማራኪ እና ተወዳጅ የቱሪስት መዳረሻ ያላት መሆኗንና በቱሪዝም ያላትን ዕምቅ ሀብት ሁሉም እንዲጎበኝ እና የውጭ ባለሃብቶችም በዘርፉ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
የዝግጅቱ ተሳታፉዎች በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች፣ ልዩ ጣዕም ያላቸው የባህል ምግቦች፣ ዘፈኖች ባለቤት፣ የሰው ዘር መገኛ፣ የተፈጥሮ ጸጋ የተቸረች እንደሆነች በአጠቃላይ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶቿን ለማወቅና ለመረዳት መድረኩ ጥሩ አጋጣሚ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል። በመሆኑም አገሪቱ ስላሏት የቱሪዝም መስህብ መረዳታቸውንና በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው ጉብኝት ለማድረግ ፍላጎት እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ አገራችን በታሪክ፣ በባህልና በተፈጥሮ ያላትን የቱሪዝም ሀብት የሚያሳዩ አጫጭር ቪዲዮዎችን በማሳየት የማስተዋወቅና ግንዛቤ የመፍጠር፣ የቡና ቅምሻ ስነ-ስርዓት፣ የብሄር-ብሄረሰቦችና ህዝቦች ዘፈንና ውዝዋዜዎች፣ የባህል ምግቦች፣ የአገራችን አልባሳትና ጌጣጌጦች የሚያስተዋውቅ ፕሮግራም ለታዳሚዎች ቀርበዋል።
በመርሃ-ግብሩ ላይ ከ130-150 ሰዎች በዋሽንግተን ዲሲና አከባቢው የሚኖሩ አሜሪካዊያን፣ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን፣ ዲፕሎማቶች፣ አርቲስቶችና የጥበብ ባለሙያዎች ታዳሚ ሆኖዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *