በመላው ዓለም ከሚገኙ የዳያስፖራ ወጣት ተወካዮች ጋር በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ውይይት ተካሄደ (June 14, 2021)
በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲና በኢፌዴሪ ሚሲዮኖች አስተባባሪነት በመላው ዓለም ከሚገኙ የዳያስፖራ ወጣት ተወካዮች ጋር በሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የመከረና በአይነቱ የመጀመሪያው የሆነ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ።
በውይይት መድረኩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢፌዴሪ ም/ጠ/ሚ እና የወ/ጉ/ሚ ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ ሁሉን አሳታፊ በሆነ ለውጥ ውስጥ እንደምትገኝ ገልጸው፣ ይኽው የለውጥ ሂደት በስኬት እንዲጠናቀቅ ወጣቶችን ጨምሮ ሁሉም ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ አሳስበዋል። አክለውም ኢትዮጵያ ከያቅጣጫው ፈተና ቢበዛባትም በጽናት ወደፊት በመራመድ ላይ እንዳለች ጠቅሰው፣ ፈተናዎቹ የህዝቡን አንድነት ይበልጥ እያጠናከሩት መምጣታቸውን ገልጸዋል። የፈተኛዎቹ መብዛት ኢትዮጵያ ሁሉንም አቅሞቿን አስተባብራ እንድትጠቀም የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው፣ ይህ ትውልድም እንደቀደምት አባቶቹ ታሪክ ሰሪነቱን የሚያሳይበት ወቅት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በተለይም ወቅቱ በሃገራችን ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ሚና የሚኖራቸውን ነጻና ሁሉን አሳታፊ ምርጫን እንዲሁም ሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሌት የሚከናወንበት መሆኑን አስታውሰው፣ ከዚህ አንጻር በሃገራችን ላይ እየተሰነዘሩ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመቋቋም የዳያስፖራ ወጣቶች የሚያከናውኑት የተደራጀና ፈጣን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ወቅታዊና አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል። በመሆኑም ይህንን አስቸጋሪ ጊዜ በስኬት መሻገር እንዲቻል ሚሲዮኖችና የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ፈተናውን የሚመጥን ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው፣ ወጣቱም የተናበበ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ሊያከናውን እንዲሁም ሁሉም አካላት በቃላቸው መሰረት ለመገኘት ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለተሳታፊዎቹ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊትም በበኩላቸው ዳያስፖራው ለሃገሩ አለኝታ መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ሃገራዊ ፕሮጀክቶችንና ጥሪዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ሃብት አሰባስቦ እየላከ በመሆኑ ምስጋናቸውን ገልጸዋል። በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዘርፍም ዳያስፖራው የኢትዮያን ገጽታ ለማጠልሸትና ያልተገባ ጫና ለማሳደር የሚንቀሳቀሱ አካላትን በመቃወም ታላላቅ የተቃውሞ ሰልፎችን፣ የትዊተር ዘመቻዎችንና የማግባባት ስራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መታየታቸውን አንስተዋል። ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም የዳያስፖራው አንድ ክፍል የሆነውን ወጣት ዳያስፖራ በማሳተፍ የተጠናከረ የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን በተጠናከረ ሁኔታ መስራት እንዲቻል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ ላይ በፓናሊስትነት የቀረቡ ክቡራን አምባሳደሮችም በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ያልተገቡ ጫናዎችን ለመከላከል በሚያስተባብሯቸው ሚሲዮኖች እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አስረድተዋል። ክቡራን አምባሳደሮቹ አክለውም ወጣት ዳያስፖራዎች ካላቸው የቴክኖሎጂ ቀረቤታና በሚኖሩበት ሃገር ከሚገኙ ሰዎች ጋር የፈጠሩትን ቅርበትና ማህበራዊ ትስስር ተጠቅመው ያለማመንታት የኢትዮጵያን እውነት ለማስረዳትና በየሃገሩ የኢትዮጵያ ወዳጆችን ለማብዛት፣ ከሚዲያ አካላትም ጋር በቅርበት ለመስራት ጥረት ሊያደርጉ እንደሚገባና ከዚህም አንጻር የሚመሯቸው ሚሲዮኖች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። በህብረትና በመናበበ እስከተሰራ ድረስ ውጤት ማግኘትና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መቀየር እንደሚቻልም ገልጸዋል።
የዳያስፖራ ወጣቶችም በበኩላቸው በያሉበት አካባቢ በማከናወን ላይ ያሉትን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ያቀረቡ ሲሆን፣ ጥረታቸው በተሻለ ውጤት እንዲታጀብ አደረጃጀቶቻቸውን ማጠናከርና ወደፊት ወጥተው መስራት እንዳለባቸው፣ የሃገር ገጽታ ግንባታ ትኩረታቸው ሊሆን እንደሚገባና በስሜት ሳይሆን በዕውቀትና በምክንያታዊነት መንፈስ መስራት እንዳለባቸው እንዲሁም ኢትዮጵያ ከእነሱ የምትፈልገውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
መድረኩ ሲጠቃለል ክብርት ዋና ዳይሬክተር ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቶች በሃገራቸው ጉዳይ ላይ በጋራ ለመስራት ስላሳዩት መነሳሳት አመስግነው፣ ወጣት ዳያስፖራዎች ሃይላቸውን አስተባብረውና አንድነታቸውን አጠናክረው ከሰሩ በሁሉም ዘርፍ የሃገራቸውን ጥቅም ማስከበር እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።
በመድረኩ ላይ ከ400 በላይ የኢፌዴሪ ሚሲዮኖችን የወከሉ ክቡራን አምባሳደሮች፣ የሚሲዮን መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች እንዲሁም የወጣቶች ዳያስፖራ ተወካዮች ተገኝተዋል።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!