በሶስቱ አገሮች ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንቲስቶች ቡድን ባዘጋጀው የውሃ ሙሌት መርሃ ግብር መሰረት የግድቡ ሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንደሚካሄድ ተገለጸ፣ (May 22, 2021)
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን በኦታዋ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ኤምባሲ እና ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ጥምረት በካናዳ በጋራ ባዘጋጁት የዌብናር ስብሰባ ላይ የህዳሴ ግድብን አስመልክተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ክቡር አቶ ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኃይል ችግር ለመቅረፍና የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የውሃ ሀብቷን መጠቀም ግዴታ በመሆኑ፣ የታችኞቹን የተፋሰስ አገሮች በማይጎዳ መልኩ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል። አያይዘውም ኢትዮጵያ ለናይል ወንዝ 86 በመቶ ድርሻ ያላት እንደመሆኗ መጠን የህዳሴ የግድብ ግንባታን በዚሁ አግባብ መጀመሯን አስታውሰዋል፡፡
ከግድቡ ጋር ተያይዞ በግብጽና በሱዳን በኩል የሚነሱ ስጋቶችን ለመቅረፍ በሶስቱ አገሮች መካከል እ.ኤ.አ በ2015 በተፈረመው የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መሰረት ውይይቶች መካሄዳቸውን ጠቅሰው፤ መፍትሔ ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይም በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት ተከታታይ ድርድሮች መደረጋቸውን አብራርተዋል። ግድቡ የታችኞቹን የተፋሰሱ አገሮች የጎላ ጉዳት እንደማያመጣ የሚታወቅ ቢሆንም በሱዳን እና በግብጽ በኩል ግን ጉዳዩን አለም አቀፍ መልክ እንዲይዝ በማድረጋቸው በአፍሪካ ህብረት አስተባባሪነት የሚካሄደውን ድርድር እያደናቀፉ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁለቱም አገሮች በጋራ እና በፍትሃዊነት ከመጠቀም ይልቅ የቅኝ ገዥዎችን ስምምነት ለማጽናት ያላቸው ፍላጎት ለድርድሩ ሂደት ተግዳሮች እንደሆኑም አስረድተዋል፡፡
አሁንም በአፍሪካ ህብረት አስተባበሪነት የሚደረገወው የሶስትዮሽ ድርድር በውሃ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ አተኩሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ ስምምነት ባለመፈረሟ የድርድር ሂደቱን እንዳስተጓጎለች የሚቀርበው ክስ መሠረት ቢስ መሆኑን ገልጸው፤ አጠቃላይ የውሃ ሀብት ክፍፍልን የሚመለከቱ ጉዳዮች ሁሉንም የናይል ተፋሰስ አገሮች የሚመለከት ጉዳይ እንደሆነ አብራርተዋል። ሁለቱ አገሮች አገራችን የወደ ፊት ውሃ የመጠቀም መብትን የሚገድብ አስገዳጅ ውል እንድትገባ የሚያደርጉት ግፊት ተገቢነት እንደሌለውም አስረድተዋል፡፡
በመርሆች ስምምነት መሰረት የውሃ ሙሌቱ የግንባታው አካል በመሆኑ እንዲሁም በሶስት አገሮች ብሄራዊ ገለልተኛ የሳይንትስቶች ምርምር ቡድኖች በቀረበውና የውሃ አሟላል መርሃ ግብር ስምምነት መሰረት ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ እንደሚከናወን አረጋግጠዋል፡፡
በካናዳ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክብርት ናሲሴ ጫላ በበኩላቸው በሚድያዎች ግድቡን በተመለከተ የሚተላለፉ የተዛቡ መረጃዎች ለማረም፣ ወቅታዊ የግድቡ ድርድር ያለበትን ደረጃ ላይ ግልጽነት ለመፍጠር እና ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስምምነት ለመድረስ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ መድረኩ በቂ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ለተሳታፊዎቹም የግድቡን ቴክኒካዊ ጉዳይ በተመለከተ ፕሮፌሰር ይልማ ስለሽ የድርድሩን ይዘትና በየአገሮች የሚነሱ ልዩነቶችን በተመለከተ እና ወ/ት ለምለም ፍሰሃ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!