በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ-ኢትዮጵያዉያን ጋር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል ( May 22, 2021)

በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አዘጋጅነት በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ-ኢትዮጵያዉያን ጋር በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በተገኙበት ዛሬ ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ውይይት ተካሂዷል።

ክቡር አምባሳደር ፍጹም አረጋ በውይይቱ ባስተላለፉት መልዕክት በአሜሪካ የሚኖሩ የዳያስፖራ ወገኖች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራት እና ተቋማት በኢትዮጵያ ላይ እየወሰዱት ያለውን ያልተገባ ተጽእኖ ለመቋቋም በላቀ አንድነትና ቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ኢትዮጵያን ለማዳከምና አንድነቷን ለማናጋት ከየትኛውም የውስጥም ሆነ የውጭ አካል የሚሰነዘር ትንኮሳ እና ጫና ለመመከት እንደሚሰሩ ያስታወቁ ሲሆን የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

የአቋም መግለጫ

እኛ በተለያዩ የአሜሪካ ስቴቶች የምንገኝ ኢትዮጵያዉያንና ትዉልድ-ኢትዮጵያዉያን በአሁኑ ወቅት በሀገር ዉስጥ እና በዉጭ የሚገኙ የጥፋት ሃይሎች ሀገራችንን ለማፈራረስ በማድረግ ላይ ያሉትን ከፍተኛ ጫና እና በዚህም ምክንያት የአሜሪካ መንግስት በሀገራችን ላይ የያዘዉን የተሳሳተ አቋም በሚመለከት ሰፊ ዉይይት ያካሄድን ሲሆን የሚከተለዉን የአቋም መግለጫ አዉጥተናል።

1ኛ• ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ለሚገኙ ጥቁር ህዝቦች ትልቅ ተምሳሌት የሆነ የረጅም ዘመን አኩሪ ታሪክ ያላት እና መቼም ቢሆን የውጭ ጣልቃገብነትን ፈጽሞ የማትቀበል ሉዓላዊ ሀገር እንደመሆኗ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ መንግስት በኩል የሚደረገዉ ፍትሃዊ ያልሆነ ጫና በአስቸኳይ እንዲቆም እና የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማክበር በሀገሪቱ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ ከመግባት እንዲታቀብ በአጽንኦት መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

2ኛ• ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ የነበረዉ አምባገነኑ የህወሃት ቡድን ከሶስት ዓመት በፊት በሀገራችን የተጀመሩትን ዘርፈ ብዙ የለዉጥ እርምጃዎች ለማደናቀፍ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ ቆይቶ በኖቬምበር 3/2020 የጽንፈኛው የህወሃት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ያደረሱትን አሰቃቂ ጥቃትና ጭፍጨፋ ተከትሎ መንግስት ይህንን ጥቃት ለመቀልበስ ወደማይፈልገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ለመግባት መገደዱ ይታወቃል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዉጭ የሚገኙ የሕወሃት ርዝራዦችና ተላላኪዎች ከሀገራችን ጠላቶች ጋር በማበር የአገራችንን ስም የሚያጠለሹና የተሳሳቱ መረጃዎችን በሚዲያ በስፋት በማሰራጨት የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በአሜሪካ የምንገኝ ኢትዮጵያውያንና ትዉልድ-ኢትዮጵያውያን ይህንን በመገንዘብ ስለሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ትከከለኛው መረጃ ለሚመለከታቸዉ አካላትና ለሚዲያ እንዲደርስ በማድረግ ይህንን የሀሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ለማጋለጥ እንደምንሰራ ቁርጠኛነታችንን እናረጋግጣለን፡፡

3ኛ• የሀገራችን አለኝታ የሆነዉ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እና የሁለተኛዉ ዙር የዉሃ ሙሌት በተያዘለት ጊዜ ዉስጥ እንዳይሳካ ለማደናቀፍ ሀገራችንን ለማዳከም የሚሰሩ ሃይሎች በእጅ አዙር የሚያደርሱትን ጫና አጥብቀን እንቃወማለን፤ ይህንንም ጫና ለመመከት እስከመጨረሻዉ ድረስ በጋራ እንቆማለን፡፡

4ኛ• በአሜሪካ በተለያዩ ስቴቶች የምንገኝ ትዉልድ-ኢትዮጵያውያን በየአካባቢያችን የሚገኙ የአሜሪካ መንግስት የስቴት እና የፌደራል ባለስልጣናትን፣ የኮንግረስ አባላትን እና ሴናተሮችን በማነጋገር (እንዲሁም የጽሁፍ መልዕክቶችን በመላክ) በሀገራችን ያለዉን ትክክለኛ ገፅታ እንዲገነዘቡ እና በሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመመራት የተሳሳተ አቋም እንዳያራምዱ በማድረግ እንዲሁም ሰሞኑን የአሜሪካ ሴኔት ያወጣውን ሪዞልሽን መልሶ እንዲያጤነው እና የኢትዮጵያና አሜሪካ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከየትኛውም ጊዜ የተሻለ እንዲሆን ጠንክረን እንደምንሰራ እናረጋግጣለን፡፡

4ኛ• ሀገራችንን ከድህነት በማላቀቅ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማረጋገጥ የዉጭ ምንዛሪ ገቢ የሚኖረዉ ሚና ወሳኝ በመሆኑ በተለይ ከምዕራባዉያን ሀገሮች የሚገኘዉ ድጋፍ በቀነሰበት በአሁኑ ወቅት በዉጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትዉልድ-ኢትዮጵያውያን ገንዘባችንን ወደ ትዉልድ ሀገራችን በህጋዊ መንገድ በመላክ እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሳተፍ የኢትዮጵያን ልማት ለመደገፍ ከፍተኛ የሆነ ተሳትፎ እናደርጋለን፡፡

5ኛ• ሀገራችን በቅርቡ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ለማካሄድ ወደ ማገባደጃ ምእራፍ በተቃረበችበት በዚህ ወሳኝ ወቅት ሆን ተብሎ ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት የሀገራችንን ሰላም ለማደፍረስ እና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በውጭና በሀገር ውስጥ የጥፋት ሃይሎች የሚደረገዉን ዘመቻ ለመመከት አንድነታችንን አጠናክረን ከመቼዉም ጊዜ የበለጠ በጋራ ለመስራት ቁርጠኝነታችንን እናረጋግጣለን፡፡

6ኛ. ጠላት የሚገባው በተከፈተ በርና መስኮት ነው። በሩንና መስኮቱን ለመክፈት በየፊናችን ስንሰራ ቆይተናል። በዚህም ክፉኛ የጠላት ኢላማ ውስጥ ገብተናል። ጥቃት እየተሰነዘረብን ነው። ይህንን አገር የማፍረስ ጥቃትን ለመከላከል መሃል መንገድ ሊኖር አይገባም። ያለው አማራጭ ወይ ከእነሱ ወይም ከእኛ መሆን ነው። ከዚህ አንጻር የውጭ ጠላት ሲመጣ አንድነት ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው ብለን እናምናለን።

7ኛ. በአደዋ ጦርነት ላይ ድል ያገግኘነው ኢትዮጵያ ያለመሪ እና ያለመንግስት ዘምታ አይደለም። ዛሬ ግን ኢትዮጵያን ለማዳን ያለመንግስትና ያለመሪ የሚሞከረው ሙከራ ለድክመት ዳርጎናል። ስለዚህ መንግስት እንደ ምሶሶ፤ ሕዝብ እንደ አጥር፤ ድርጅቶች፤ አክቲቪስቶችና ምላው የዳያስፖራ ማህበረሰብ ቋሚና ማገር ሆነን ለኢትዮጵያ አገራችን በአንድነት ለመቆም ተነስተናል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም

ዋሽንግተን ዲሲ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *