አቶ ደመቀ መኮንን ከካዛኪስታን እና ከሰርቢያ የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከካዛኪስታን እና ከሰርቢያ የምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ተወያዩ። በአዘርባጃን ባኩ ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ ጉባኤ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ደመቀ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች አገራት ጋር የሚኖራትን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ አገራት ጋር ተወያይተዋል። የካዛኪስታን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካኔት ቱመሽ በኢትዮጵያ በመንግሥት በኩል የተካሄዱ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ለውጦችን አድንቀዋል። ካኔት ሀገራቸው በቱሪዝም እና በኢንሸስትመንት አቅሞች ላይ በጋራ ለመሥራት ፍላጎት እንደላትም ገልጸዋል። ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በቢዝነስ ሥራዎች የተሰማሩ ባለሀብቶች በካዛኪስታን ጉብኝት እንዲያደርጉ እና ትሥሥራቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል። እንዲሁም ካዛኪስታን ለተማሪዎች ነፃ የስኮላርሺፕ ዕድሎች እንደምታመቻችም ተናግረዋል።አቶ ደመቀ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የነበረውን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት በሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በውስጥ አቅም ችግሮችን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችና ወደ ተግባር የተገባበትን ሂደት አስረድተዋል።

የሁለቱን አገሮች የንግድ እና የቢዝነስ ትብብር በሚፈለገው ደረጃ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል።ካዛኪስታን እ.ኤ.አ በ2017/2018 በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የተለዋጭ ቋሚ ኮሚቴ አባል በነበረችበት ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ስትሠራ እንደነበርም አስታውሰዋል። በተመሳሳይ አቶ ደመቀ ከሰርቢያ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አይቨክ ዳሴክ ጋር ውይይት አድርገዋል።በውይይታቸውም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ጠንካራ ታሪካዊ ግንኘነት ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን ኢዜአ ዘግቧል። ካዛኪስታን እና ሰርቢያ የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ አባል ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲ በትብብር ይሠራሉ።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *