እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል አደረሳችሁ! (January 6, 2021)

የዘንድሮውን የልደት በዓል የምናከብረው በዚህ ዓመት ያሳለፍነውን ፈታኝ ተጋድሎና ከፊታችን የሚጠብቀንን ወሳኝ ዕድል እያሰብን ነው። አሁን በፈተናና በዕድል መካከል እንገኛለን። ዓለምም የመጀመሪያውን የክርስቶስ ልደት ያከበረችው በፈተናና በዕድል መካከል ሆና ነበር። በአዳም በደል ምክንያት የመጣው የመከራ ዘመን እያለፈ፤ የመከራው ዋና ምንጭ የሆነው ዲያብሎስ፣ በማኅጸን በተጀመረ የማዳን ሥራ እየተሸነፈ፤ የጨለማው ንጉሥ እየተረታ፤ የዘመናት ቋጠሮ እየተፈታ ነበር። ከፊት ደግሞ የመዳን፣ የብርሃን፣ የሰላም፣ የነጻነት እና የፍቅር ዘመን እየመጣ ነበር።

ነገሩ ግን ሂደቱ ቀላል አይደለም። የጨለማው ዘመን አበጋዞች እንዲነጋ አልፈለጉም። ሊመጣ ያለው ድኅነት የማያስቀሩት ቢሆንም እንኳን፤ የሚያሸንፉት እስኪመስሉ ድረስ ተፍጨርጭረዋል። እየበራ ያለውን መብራት የሚያጠፉት ያህል ታግለዋል። የተከፈተውን የብሩኅ ተስፋ መስኮት የሚከረችሙት ያህል ፎክረዋል። የተሸነፈውን ዘንዶ ዳግም ሕይወት የሚዘሩለት ያህል ተገዳድረዋል። ግን ይህ ሁሉ አልሆነም።

ሄሮድስ ተነሥቶ ነበር። ብዙዎችንም በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል። ዘመኑም የብሩኅ ተስፋ ሳይሆን የመከራ ዘመን መስሎ ነበር። በክርስቶስ መወለድ የተፈጠረው ደስታ፣ በቤተልሔም ሕጻናት ግድያ የደበዘዘ እስኪመስል። በበረት ውስጥ የተፈጠረው ተስፋ፣ በድንግል ማርያምና በክርስቶስ መሰደድ ያበቃለት እስኪመስል። በመላእክት ዝማሬ የተበሠረው አዲስ ዘመን፣ በሄሮድስ አበጋዞች ጭፍጨፋ ሕልምና ተረት እስኪመስል። የኦሪት ዘመን አበቃ ሲባል፤ በኦሪት ዘመን የማይሠራ ግፍ፣ በዘመነ ሐዲስ በቤተልሔም ከተማ ተከሠቷል። ብዙዎችንም ተስፋ አስቆርጧል።

ቢሆንም መከራው አላፊና ጠፊ እንጂ ዘላቂ አልነበረም። ያ እንደ ተራራ የገዘፈ የመሰለው ሽብር እንደ እንቧይ ካብ የሚፈርስ፤ እንደ ባሕር የሰፋ የመሰለው መከራ እንደ መጋቢት ወንዝ የሚነጥፍ፤ የማይሸነፉ የሚመስሉት ሁሉ እንደ ጎልያድ የሚወድቁ፤ አስጨናቂዎች ሁሉ መልሰው የሚጨነቁ መሆናቸውን – ያሳየ አጋጣሚ በዚያን ዘመን ተከሥቷል። ለዚያም ነው ሁሉም አልፎ ዛሬ ድረስ የልደትን በዓል ልዩ ትርጉም ሰጥተን የምናከብረው።

ውድ የሀገሬ ሕዝቦች፣

አሁን ኢትዮጵያ በልደቱ ቀን ቆማ ልደትን የምታከብር ሀገር ናት። ተስፋዋን፣ ሰላሟን፣ ንጋትና ብልጽግናዋን እንዳታይ በዙሪያዋ የቆሙ የሄሮድስ አበጋዞች አሉ። በቻሉት መጠን መከራችን እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። የተወለደልንን የተስፋ ብርሃን ለመግደል ይጥራሉ። ከተማዋን የዋይታ ከተማ ለማድረግ ይለፋሉ። ነገን እንዳናይ መስኮቶችን ሁሉ ይዘጋሉ። ወደ ተስፋ መጠጊያ ዋሻችንን በቋጥኝ ደፍነው በቀቢጸ ተስፋ ውስጥ እንድንቆይ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ።

ሆኖም ግን ፈተናችንን ያበዙብን ሄሮድሶች ከብልጽግና መንገዳችን አያስቀሩንም፤ እስከ መጨረሻው ሕቅታቸው ወደ ኋላ ሊጎትቱን ቢጥሩም ጨርሶ ከጉዟችን ሊያስቆሙን አይችሉም። በመንገዱ ላይ የዘሩትን አሜከላ እየለቀምን፣ እንቅፋትና ጋሬጣውን ተሻግረን ከተራራው እናት መውጣታችን አይቀርም። የተሰበረውን ድልድይ ጠግነን፣ ከችግሮቻችን በላይ ከፍ ብለን ያለጥርጥር ኢትዮጵያን ወደ ተስፋዋ አድማስ እናደርሳታለን።

ገና ያኔ የለውጥ ጉዟችን ሲወለድ ጀምሮ ተመሳሳዩን ሲያደርጉ ነበር። በየወቅትና አጋጣሚው ጉዟችን እንዲሰናከል ያልወረወሩት ድንጋይና ያልጣሉት ጋሬጣ አልነበረም። ከመንገዳችን ሳንሰናከል ገፍተናል፤ በፈተናዎቻችን ትምህርት፣ በችግሮቻችን ጥንካሬ፣ በእንቅፋቶቻችን ብርታት እያገኘን ዛሬ ላይ ደርሰናል። ከእያንዳንዱ ጨለማ ወዲያ ንጋት መኖሩን እያመንን፣ ዐይናችንን ወደ ወጋጋኑ አቅንተን ጉዟችንን ቀጥለናል። እኛ አንድ ወደ ፊት በተራመድን ቁጥር ችግሮቻችን ወደኋላ ይሸሻሉ፤ እኛ ይበልጥ በበረታን ቁጥር እነሱ ይሸነፋሉ።

ያም ሆኖ አንድ ልብ ሊባል የሚገባው እውነት አለ። ለኢትዮጵያ የፈነጠቀውን የተስፋ ብርሃን ከእንግዲህ ማንም ሊያጠፋው አይቻለውም ሲባል እስከናካቴው አይሞክርም ማለት አይደለም። የሄሮድስ ወታደሮች ሕጻኑን ክርስቶስ እስከ ግብጽ ድንበር ድረስ እንደተከታተሉት ሁሉ ፈታኞቻችን ነገም ይከተሉናል።

እንቅፋቶቻችን መልካቸውን እየቀያየሩ በመንገዳችን ላይ መቆማቸውን ይቀጥላሉ። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ የትንሣኤ ጉዞ ፍጥነቱ ከምንም በላይ የሚወሰነው በእኛ ጥንካሬ እንጂ በእነሱ ችግር ፈጣሪነት መጠን አይደለም፤ መሆንም የለበትም።

እኛ እስካልፈቀድንላቸው ድረስ ለሀገራችን የተወለደውን ተስፋ ሊያመክኑት፣ የተለኮሰውን ፋና ሊያጠፉት አይችሉም። ጨልሞባት የነበረችው ሀገራችን ምሽቷ መንጋት ጀምሯል – እኛ ከበረታን ዳግም በእነሱ ሤራ አይጨልምም። ያጎበጣት የዘመናት ፍዳ አንዴ መደርመስ ጀምሯል – እኛ ችላ እስካላልን ድረስ ዳግም አይቆለልም። ከእንግዲህ የኢትዮጵያ ስኬትና ውድቀት ማዕከሉ የእኛ ጥንካሬና ድክመት ነው ብለን ማመን አለብን።

ውድ ወገኖቼ፣

ከተስፋችን አንጻር ፈተናችን ብዙ ባይሆንም ወደፊት ይበልጥ መፈተናችን እንደማይቀር ማወቅ አለብን። ወደ ተስፋ በተጠጋን ቁጥር የመከራው ብርታት እንደሚጨምር ያለፉት ሦስት ዓመታት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው። በመከራ ውስጥ ከሚመጣ መከራ ይልቅ በተስፋ ውስጥ የሚመጣ መከራ እጅግ ይከብዳል የሚባለውም ለዚህ ነው። በአንድ በኩል ልቡና ተስፋ እያደረገ ፈተና ሲገጥመው ያማርራል። በመከራ ውስጥ ሆኖ መከራ ሲገጥመው ግን ‹የበሰበሰ ዝናም አይፈራም› እንደሚባለው በአማራጭ ማጣት ይታገሣል። በተስፋ ውስጥ ፈተና የሚያጋጥመው ሰው ግን እምነት ያጣል። አእምሮው ለሐሴት እንጂ ለሑከት አልተዘጋጀም። ከትግል ጊዜ ይልቅ በድል ጊዜ ብዙዎች ይሞታሉ የሚባለው ለዚህ ነው። በትግል ጊዜ የነበራቸው የመሥዋዕትነት ሥነ ልቡና በድል ጊዜ አይገኝም።

ኢትዮጵያ ሁለቱም ያጋጥማት ይሆናል። ተስፋ ባነገበች ሀገር ላይ ተስፋ መቁረጥ፤ ሰላም ባነገበች ሀገር ላይ ግጭት፤ ብልጽግናን ባነገበች ሀገር ላይ ውድመት ይመጣባት ይሆናል። መነሻችን ‹አያዎ› ነው – ‹አይ እና አዎ›። መድረሻችን ግን ‹አዎ› ብቻ ነው። ብርሃን ጨለማን፤ ሰላም ጦርነትን፣ ፍቅር ጥላቻን፤ አንድነት መለያየትን፣ ብልጽግና ኋላቀርነትን ማሸነፋቸው አይቀሬ ነው። በልቅሶ የሚዘሩ በደስታ ማጨዳቸው የማይቀር ነው።

ከወፍ ዕንቁላል ውስጥ ጠንካራው ቅርፊቱ ነው። ጫጩቷ ቅርፊቱን ሰብራው ከወጣች በኋላ ግን ጠንካራ መሆኑ ያበቃል። ጫጩቷ ታድጋለች፤ ቅርፊቱ ግን በተቃራኒው መፈራረስ ይጀምራል። ጫጩቷ ትበራለች፤ ቅርፊቱ ዱቄት ይሆናል፤ ብሎም ይበሰብሳል። ጫጩቷ ወፍ ሆና ሌሎች ዕንቁላሎች ትጥላለች፤ ሌሎች ጫጩቶችንም ትፈለፍላለች። ቅርፊቱ ግን ይበልጥ እየበሰበሰ ወደ አፈርነት ይለወጣል። የኢትዮጵያም ችግሮች እንደዚሁ ናቸው። ለጊዜው ጠንካራና ዙሪያችንን ከብበው የያዙን ይመስላሉ። ይህ የሚሆነው ግን እስክንሰብራቸው ድረስ ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ እኛ ከችግሮቻችን መብለጣችን አይቀሬ ነው።

ከክርስቶስ ልደት የምንማረው ይሄንን ነው። የትናንቱ ሲያልፍ ዝም ብሎ አያልፍም። የመጨረሻ ሙከራውን አድርጎ ነው የሚያልፈው። ልክ እንደሄሮድስ ሙከራ። የነገውም ዝም ብሎ አይመጣም፤ በተጋድሎ ነው የሚመጣው። ልደት ግን በሚያልፍ መከራና በሚመጣ ዕድል መካከል መሆኑ አይቀሬ ነው። ኢትዮጵያም እያለፈችው በምትሄደው መከራና፣ እያገኘችው በምትመጣው ዕድል መካከል ናት።

‹ዛሬ› በትናንትና በነገ መካከል ስለሆነ የሁለቱም መልክ ይታይበታል። ከትናንት የወረሰው መከራ፤ ከነገ የተዋሰው ደስታ አለው። ንጋት ማለት በሚያልፍ ጨለማና በሚመጣ ቀን መካከል ነው። መሽቷል ያለ ይተኛል፤ ነግቷል ያለ ይነሣል። የእኛም ምርጫ ይሄው ነው። መሽቷል ብለን እንተኛለን ወይስ ነግቷል ብለን እንነሣለን?

መልካም የልደት በዓል ይሁንልን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ታኅሣሥ 28፣ 2013 ዓ.ም

No photo description available.
Image may contain: text
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *