የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ መጋቢት 20/2015(ኢዜአ)፦የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሀገራዊና ሁለትዮሽ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱንም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ታዜር ገብረእግዚአብሔርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተፈራርመዋል።
አቶ ታዜር በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከዕለታዊ ስራዎች ጀምሮ በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር በጋር ይሠራሉ።
የመግባቢያ ስምምነቱ የትብብር ሥራዎቹ ስርዓት የያዙና በሰነድ የተደገፉ እንዲሆኑም ያግዛል ብለዋል።
ስምምነቱ ሀገራችን ከተለያዩ ሃገራት ጋር የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚረዱ ተግባራትን ለማጠናከር እንደሚያስችላት አቶ ታዜር አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሁለቱ ተቋማት ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በጋራ ለማመንጨት የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸውም ገልጸዋል።
አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በበኩላቸው ሁለቱ ተቋማት የተሰጣቸውን ተልዕኮ በመፈፀም በኩል በሥራ የሚገናኙባቸው ጉዳዮች በርካታዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጪ ቢሮም ጭምር በመጋራት በትብብር የሚወጧቸው ተልዕኮዎች መኖራቸውንና በተለያዩ የሥራ እንቅስቃሴዎችም የመረጃ ልውውጥ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
የእስከ አሁኖቹ የጋራ ሥራዎች ስኬቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በሁለቱ ተቋማት አመራሮች ቁርጠኝነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የነበረውን የትብብር ግንኙነት በሰነድ የተደገፈ ለማድረግ የመግባቢያ ስምምነቱ መፈረሙን ገልጸዋል።
ስምምነቱ ዲፕሎማቶች የሀገር ጥቅምና ብሔራዊ ደኀንነት በማስጠበቅ ረገድ በቂ ዝግጅት እንዲኖራቸው ከብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሚያገኟቸውን የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንደሚያጠናክር አብራርተዋል።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!