የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የውሃ ጉባዔ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

መጋቢት 13/2015 ዓ.ም. (ው.ዒሚ.) የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ በኒውዮርክ እየተካሄደ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት የውሃ ጉባዔ እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ክቡር ሚኒሰትሩ ከ50 ዓመት በኋላ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንዲሁም በታጂክስታንና በኒዘርላንድስ መንግስት አዘጋጅነት ዛሬ በጀመረውና እ.አ.አ ከማርች 22 – 24 ቀን 2023 ለሶስት ቀናት በኒውዮርክ ከተማ በሚካሄደው አለምአቀፍ የውሃ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያን በመወከል እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

የጉባዔዉ ዋና ዋና የመወያያ ርእሰ ጉዳዮች ውሃ ለጤና፤ ውሃ ለዘላቂ ልማት፤ ውሃ ለአየር ንብረት እና አካባቢ፣ ውሃ ለትብብር የመሳሰሉት ሲሆኑ፤ በሶስት መድረኮች ማለትም፤ ውሃ ለዘላቂ ልማት፤ ውሃ ለአየር ንብረት እና አካባቢ እና ውሃ ለትብብር በሚሰኙት መድረኮች ላይ የኢትዮጵያ ልኡካን ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።
ክቡር ሚኒስትሩ በኒውዮርክ በሚኖራቸው ቆይታ፤ ንጹህ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ለሁሉም የሚለው ዘላቂ የልማት ግብን በተመለከተ፤ ድርቅና የአየር ንብረት ለውጥ እንደሀገር ያስከተለውን ተጽእኖ በሚመለከት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ፋይዳንና ድርቅን የሚቋቋም የግብርና ስራዎችን በተመለከተ፤ እንዲሁም የውሃ ሀብትን በትብብር መጠቀምን አስመልክቶ ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡
በመድረኩ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋን ጨምሮ፤ ክቡር ዶ/ር ኢ/ር ስለሺ በቀለ – በአሜርካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ አቶ ፈጠነ ተሾመ-የኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጂ ኢንቲትዩት ዳይሬክተር ጄነራል፤ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ- የተመድ ቋሚ መልዕክተኛና ባለ ሙሉ ሥልጣን አምባሳደር፣ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *