ጨረቃ ላይ ውሃን ለማግኘት እንዲሰራ ኃላፊነት የተሰጠው ኢትዮጵያዊ የናሳ ተመራማሪ-ዶክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ቡልቻ
ወደ አሜሪካ ስመጣ የሚደግፈኝ አልነበረም፣ ነገር ግን ትልቅ ህልም ነበረኝ፡- ጨረቃ ላይ ውሃን ለማግኘት ላይ የሚሰራው ኢትዮጵያዊ የናሳ ተመራማሪ
ኢትዮጵያዊው የናሳ ተመራማሪ ዶክተር ኢንጂነር ብርሃኑ ቡልቻ በጨረቃ ላይ ያለውን ውሃ የመለየት ችግር መፍትሄ ለመስጠት ከቡድን አጋሮቹ ጋር በመስራት ላይ የሚገኝ ሳይንቲስት ነው፡፡
ተመራማሪው ከዚህ በፊት ጨረቃ ላይ ውሃ ለማግኘት የሚያስችል በመጠን አነስተኛ የሆነ ቁስ የኳንተም ፊዚክስ ቀመርን በመጠቀም መስራቱ የሚታወስ ሲሆን ይህን ምርምሩን ከግብ ለማድረስም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
“ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ስመጣ የባህል ልዩነቱ እና የሚደግፈኝ ባለመኖሩ ተቸግሬ ነበር” የሚለው ኢንጂነር ብርሃኑ፤ “ሁሌም የማስበው ጠንክሮ መሥራት እና በትምህርት ስኬታማ መሆንን ነበር” ይላል፡፡
በልጅነቱ መጽሐፍ ቅዱስ ሲያነብ ስለ አጽናፈ ዓለም/Universe/ አፈጣጠር እና ተያያዥ ክስተቶች ያነበባቸው ታሪኮች ስለ ህዋ ይበልጥ ጥያቄዎችን እንዲጠይቅ እና ምርምር የማድረግ ፍላጎት እንዲያድርበት ማድረጉን ለቢቢሲተናግሯል።
“በውስጤ ነገሮች እንዴት ተፈጠሩ የሚለው በጣም ያስደንቀኝ ነበር፤ ዩኒቨርስ ምን እንደሚመስል እና ምን ያህል ትልቅ እንደሆነ የበለጠ ለማወቅ ትልቅ ጉጉት ነበረኝ” ሲልም ይገልፃል።
በልጅነቱ ለማወቅ እና ለመስራት በሚያልመው የህዋ ምርምር ዘርፍ ላይ ከብዙ ጥረት በኋላ የደረሰው ኢንጂነር ብርሃኑ፣ አሁን ላይ በጨረቃ ላይ ያለውን ውሃ የመለየት ችግር መፍትሄ ለመስጠት እና ሰዎች ጨረቃ ላይ መኖርን እንዲያልሙ የሚያስችል አስደናቂ ምርምር በማድረግ ላይ ይገኛል።
ከሰሞኑ በሜሪላንድ የሚገኘው የናሳ ጎዳርድ የጠፈር በረራ ማእከል ኢንጂነር ብርሃኑ በዚሁ የምርምር ማዕቀፍ ውስጥ ያበለፀገውን ፕሮቶታይፕ ለማጠናቀቅ እንዲያስችለው 2.5 ሚሊዮን ዶላር ፈንድ እንዳቀረበለት የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።
በዚህ ፕሮቶታይፕ ላይ የሚሰራውን የቴክኒካል ስራ ለማጠናቀቅ ሌላ ሁለት ዓመት ሊፈጅ ቢችልም የተጀመረው ስራ እንደሚሳካ ኢንጂነር ብርሃኑ ያለውን ተስፋ ይገልፃል።
ውሃ ከምድር ወደ ጨራቃ ሊጓጓዝ ቢችልም ወጪው የማይቀመስ እና ስራው ውጤታማ ባለመሆኑ የኢንጂነር ብርሃኑና የቡድን አጋሮቹ ምርምር ትልቅ ውጤት የሚያስገኝ ነው፡፡
በዚህ የምርምር ዘርፍ ውስጥ ቀደም ሲል በተደረጉ ጥናቶች ጨረቃ ላይ አነስተኛ መጠን ያለው ውሃ መኖሩ ቢረጋገጥም የውሃ ውህዶችን በትክክል መለየት ግን ሳይቻል ቆይቷል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ በጨረቃ ላይ ያሉትን የውሃ አካላት ከውህዳቸው ጋር ለመለየት እና ብሎም በትክክል ቦታውን ለማመላከት የሚያግዘው የኢንጂነር ብርሃኑ የምርምር ስራ ለብዙ ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
በምርምር ስራዎች ላይ ብዙ መሰናክሎች አንደሚያጋጥሙት የሚገልፀው ኢንጂነር ብርሃኑ ሁልጊዜም ማለምን እንደማያቆም፣ በህልሙ ላይ ደግሞ አቅዶ መስራት እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!