ክቡር አምሳሳደር ስለሺ በቀለ በአሜሪካ ከሚገኙ ከ36 በላይ የዳያስፖራ አደረጃጀት ኃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ሰኔ 8/2015 ዓ.ም ውይይት አድርገዋል።

ውይይቱም በአገራችን ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች፣ የገጠሙ ፈተናዎችና መፍትሄዎቻቸው፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ወቅታዊ ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከቤተ-እምነቶች እና መኖሪ ቤቶች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጥያቄዎች፣ በአገራችን ሰላምና አንድነት የዳያስፖራው ተሳትፎ፣ በሁለትዮሽ ግንኙነትና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።

አምባሳደር ስለሺ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በአገራችን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መንግስት ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተወሰዱት እርምጃዎች ለአብነት አንስተዋል።

ከእምነት ተቋማትና ከመኖሪያ ቤቶች መፍረስ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ለኤምባሲውም በአካልና በተለያዩ መንገዶች መቅረባቸውን ጠቁመው ህግን በማስከበር ሂደት ካለፉት ክፍተቶች በመማር መንግስት ህዝቡን ያመከለ አካሄዶችን እንደሚያስቀድም ጠቅሰዋል።

አገራችን ባለፉት ጥቂት አመታት ከውስጥም ከውጭም በገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ዳያስፖራው ላበረከተው ሁሉን አቀፍ ገንቢ አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

ወቅቱ አገራችን ከነበሩባት ፈተናዎች ወጥታ ወደምትታወቅበት ሰላምና ፈጣን ልማት እንድትገባ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው ለትውልድ የሚሻገር አሻራ ለማሳረፍ ሁለም ሊረባረብ እንደሚገባም አምባሳደር ስለሺ ተናግረዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የአረብ ሊግ በተደጋጋሚ የሚያወጣቸው መግለጫዎችና አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ሳታስደፍር በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ከተመሰረተው አቋሟ ዝንፍ እንደማትል ገልጸዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም መንግስት ህግን ለማስከበር የሚወስዳቸው እርምጃዎች ንጹሃንን ለእንግልት የማያጋልጡ እንዲሆኑ፣ ለውይይት ቅድሚያ እንዲሰጥ፣ በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ እርምጃ የወሰዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ፣ የመረጃ ፍሰት እንዲጎለብት እና ሌሎች ሃሳቦች ያነሱ ሲሆን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንድሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *