” የመጪውን ትውልድ በአባይ ውሃ የመልማት መብት የሚጋፉ አቋሞችን ኢትዮጵያ አትቀበልም” – አምባሳደር ስለሺ በቀለ


(ታኀሣሥ 10 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ):-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ(ዶ/ር)፣ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ ከግብፅና ሱዳን ጋር በተደረገው አራተኛ ዙር ድርድር ዙሪያ በዛሬው እለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ኢንጅነር ስለሽ በቀለ በመግለጫቸው፣የኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር)ና የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ሐምሌ 2015 ዓ.ም የሰጡትን አቅጣጫ ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን መካከል አራት ዙር ድርድሮች መካሄዳቸውን ገልጸዋል።
አራተኛው ዙር የሶስትዮሽ ድርድር ከታህሳስ 7 እስከ 9 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየ ቢሆንም መቋጫ ሳያገኝ ተጠናቋል።
በአራቱ ዙር ድርድሮች በበርካታ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ቢደረስም ግብፅ በምታራምዳቸው ኢ-ፍትሃዊ አቋሞች ምክኒያት ቁልፍ በሆኑ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ መስማማት አልተደረሰም።

በድርድሩ ኢትዮጵያ የመርሆዎች መግለጫ ስምምነትን መሰረት በማድረግ፣ ሶስቱ ሀገራት በፍትሃዊነት፣ በምክንያታዊነት እና በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ ሁኔታ የአባይን ውሀ መጠቀም አለባቸው የሚለውን የጋራ ተጠቃሚነት አቋሟን ማራመዷን ዋና ተደራዳሪው አውስተውል።
ግብፅ በተቃራኒው የቅኝ ግዛት ዘመን አቋሞቿን ሳትቀይር የኢትዮጵያን የመጭው ትውልድ የመልማት መብት የሚጋፋ ሀሳቦችን ይዛ መቅረቧን ክቡር አምባሳደር ስለሺ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የመጪውን ትውልድ የመልማት መብት የሚጋፉ ማንኛውንም አካሄድ እንደማትቀበል ዋና ተደራዳሪው በመግለጫው አስገንዝበዋል።
ዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ህጎችንና መርሆዎችን መሰረት በማድረግ በድርድር ስምምነት ላይ ለመድረስ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *