በኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሞሐመድ እንድሪስ የሚመራ ልዑካን ቡድን በሰሜን አሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር የዳያስፖራ ዲፕሎማሲና ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማጠናከር በሚቻልበት ጉዳዮች ላይ ለመመካከር ቆይታ ያደርጋል።
ልዑካን ቡድኑ በዋሺንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተገኝተው በዳያስፖራ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲሁም በኤምባሲው የሚሰጡ የዳያስፖራ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በዛሬው እለት ውይይት አካሂደዋል።
ክቡር አምባሳደር ስለሺ የኤምባሲው ሰራተኞች በተገኙበት ለልኡካን ቡድኑ በኤምባሲው የተከናወኑ የፖለቲካ፣ የቢዝነስ፣ የዳያስፖራ ዲፕሎማሲ ሁለንተናዊ ተሳትፎ እንዲሁም በዳያስፖራ የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ዙሪያ ዝርዝር ገለፃ አድርገዋል።
ባለፉት አመታት በአገራችን የገጠሙ ችግሮችን ለመሻገር በሚደረገው ጥረትም ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከሀገራቸው ጎን በመሆን በሀገራችን ላይ ተላልፈው የነበሩ አግባብ ያልሆኑ ውሳኔዎችን ለመቀልበስ በርካታ ርብርብ ሲደረግ እንደነበር ክቡር አምባሳደር ስለሺ ባደረጉት ገለጻ ጠቅሰዋል፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የዳያስፖራ አደረጃጀቶችን በማደራጀትና በማጠናከር ለሀገራዊ ጥሪ ፕሮጀክቶች፣ በጦርነቱ አማካኝነት የተጎዱ የአገራችን ክፍሎች መልሶ ግንባታ ድጋፎችን በመሰብሰብ፣ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና የወደሙ መሰረተ-ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ ለገበታ ለትውልድ ፕሮጀከት እንዲሁም ለበጎ አድራጎት ስራዎች ከዳያስፖራው ጋር በመሆን የተሰሩ ስራዎችን አብራርተዋል።
የልኡካን ቡድን በዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው እያደረገ ባለው ቆይታም በዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ማዕከል ጉብኝት አድርጓል።
ከተቋቋመ 20ዓመታትን ያስቆጠረው በዋሺንግተን ዲሲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ማዕከል ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ የጤና ሽፋን አገልግሎት፣ የትምህርት እድሎችን ማመቻቸት፣ የአቅም ግንባታ፣ ከማህበረሰቡ የሚነሱ ችግሮችን ለመፍታት፣ እንዲሁም በርካታ ማህበራዊ ስራዎችን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ በማቅረብ አገልዕግሎቶችን እንደሚሰጥ የማእከሉ ሀላፊ የልኩካን ቡድኑ ባደረጉት ጉብኝት ገለጻ ሰጥቷል።
ማህበረሰቡን የማዕከሉ አባል በማድረግ የሚያቀርበውን አገልግሎት የልኡካን ቡድኑ አበረታተው ማዕከሉ የነዋሪዎችን ህይወት ለመቀየር በርካታ እድሎችን በማመቻቸት በተለይም የማእከሉ አባል ሆነው የጤና አገልግሎት በማመቻቸት ተጠቃሚዎች የጤና ሽፋን እንዲያገኙ የሚያደርገው ስራ እጅግ የሚበረታታ እንደሆነ ጠቅሰው የማእከሉን ከ20 አመታት በላይ ያስቆጠረ አገልግሎት ለማስቀጠል ስትራቴጂክ የሆኑ እቅዶችን በማውጣትና በመቀናጀት ቀጣይነቱን ማረጋገጥ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሞሐመድ እንድሪስ ገልጸዋል።
ከማህበረሰቡ የሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች እንዳሉ የማእከሉ ሀላፊ በጉብኝት ወቅቱ ያነሱ ሲሆን ይህንንም ለመፍታት ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ብዙ ስራዎችን ለማከናወን የተለያዩ የስትራቴጂክ እቅዶችን ማዘጋጀቱን ለልኡካን ቡድኑ አብራርቷል።
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!