በመላው ዓለም ከሚገኙ የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮች ጋር በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ (July 4, 2021)
በመላው ዓለም ከሚገኙ የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮች ጋር መንግስት በወሰደው የተናጥል የሰብዓዊ ድጋፍ ተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ የበይነ መረብ ውይይት ተካሄደ፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት ባስተላለፉት መልዕክት መድረኩ በመንግስት ከተወሰደው የተኩስ አቁም ውሳኔ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ብዥታ በማጥራት በዳያስፖራው የተጀመሩ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲሄዱ ማድረግን ዓላማ አድርጎ መዘጋጀቱን አንስተው፣ ለውሳኔው መነሻ የሆኑ ምክንያቶችን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም ዳያስፖራው ከውሳኔው ጋር በተያያዘ ያሉትን ጥያቄና አስተያየቶች እንዲሁም ቀጣይ የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አካሄድን በተመለከተ ሃሳቡን እንዲያጋራ ጋብዘዋል፡፡
የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ተወካዮቹም መጀመሪያ አካባቢ ውሳኔውን ሲሰሙ መደናገጣቸውን አንስተው፣ በተከታታይ በልዩ ልዩ የመንግስት አካላት መግለጫዎች ከተሰጡ በኋላ በጉዳዩ ላይ ግልጽነት እንድተፈጠረላቸውና ውሳኔው በበቂ ምክንያቶች ላይ የተመሰረተ እንደሆነ መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በዳያስፖራው ዘንድ የሚከናወነው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በመንግስ በኩል መከናወን አለባቸው ያሏቸውን ነገሮች አቅርበዋል፡፡ ከነዚህም መካከል መረጃዎች ወቅታዊነታቸውን ጠብቀውና ተናበው እንዲቀርቡ፣ የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት የሚያከናውኑትን ስራ የሚደግፍና በባለሙያዎች የሚመራ የህዝብ ግንኙነት ስራ እንዲከናወን፣ በሃገር ውስጥ በመንግስት የሚከናወኑ መልካም ተግባራትን ለዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግና አመለካከትን ለመለወጥ ሊሰራ እንደሚገባ መናገራቸው ይጠቀሳሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስተባባሪዎቹ በዕውቀታቸውም ሆነ በገንዘባቸው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራውን ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን አንስተው፣ በየአካባቢያቸው የሚገኙ ሚዲያዎችን በመቅረብ የኢትዮጵያን ዕውነት ለማስረዳት የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መድረኩ ሲጠቃለል ባስተላለፉት መልዕክት መንግስት በተለያዩ ገፊ ምክንያቶች ማለትም ዋነኛዎቹ የህግ ማስከበር ዓላማዎች በመሳካታቸው፣ ግጭቱ ከመደበኛ ወደ ህዝባዊ ግጭት በመለወጡና ይህም ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ እንዲሁም ወቅቱ ክረምት በመሆኑ የግብርና ስራ እንዳይስተጓጎል ማድረግ በማስፈለጉ የተኩስ አቁም ውሳኔ ላይ መድረሱን ጠቅሰው፣ ውሳኔውም የኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለማስከበር መወሰዱን አብነቶችን በማንሳት አስረድተዋል፡፡ አክለውም መንግስት የመረጃ ፍሰት ክፍተት እንዳለበት እንደሚረዳና ይህንንም ለማስተካከል አሰራሮችን ማበጀቱን ገልጸው፣ ዳያስፖራውም በአዲሱ አሰራር የሚመነጩ ወቅታዊ መረጃዎችን ከሚሲዮኖችና ከሚመለከታቸው ክፍሎች በማግኘት የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራው ግለቱን ጠብቆ እንዲሄድ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን ቸቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የኢፌዴሪ ሚሲዮን መሪዎችን፣ ዲፕሎማቶችን፣ የዳያስፖራ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አስተባባሪዎችንና አባላትን ጨምሮ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!