በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር ውይይት ተካሄደ፣ (May 18, 2021)

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት ተካሂዷል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እንዲሁም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፐብሊክ ዲፕሎማሲና ቃል-አቀባይ ዳይሬክቶሬት ጄነራል አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መድረኩን በአወያይነት መርተውታል።

በወቅቱም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የደረሰበት፣ የግድቡ የግንባታ አፈጻጸምን እንዲሁም የግቡን ህዝባዊ ተሳትፎ በተመለከተ ገለጻ ቀርቧል።

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የድንበርና ድንበር ተሻጋሪ ሀብቶች የሚኒስትሩ አማካሪ አምባሳደር ኢብራሂም እድሪስ ግብጽና ሱዳን የሚከተሉትን የውሃ ፖሊስ መነሻ በማድረግ በሰጡት ገለጻ አገራቱ በዓባይ ውሃ የበላይነትን ለመያዝ በተለያዩ ጊዚያት ያደረጉትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ገለጻ ሰጥተዋል። አገራቱ ከዓለም አቀፍ ህግ አንጻር የሚያራምዱት ፍትሃዊ ያልሆነ አቋም እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተካሄዱ የሶስትዮሽ ድርድሮችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኢንጅነር ጌዲዮን አስፋው በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገራችን የኢነርጂ ፍላጎት ያለውን ጠቀሜታ በማንሳት ግድቡ አለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እየተገነባ መሆኑንና የግድቡ ደህንነትን በተመለከተም ሶስቱም አገራት የተስማሙበት እንደሆነ አንስተዋል።

ለግድቡ የተደረገውን ህዝባዊ ተሳትፎ በተመለከተም ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ሁለንተናዊ ድጋፍ መቀጠሉንና እስካሁንም ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በአገር ከአገር ውስጥና ከውጭ ድጋፍ መሰባሰቡን አቶ ሄኖክ ገልጸዋል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ም/ቤት ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ ታሪካዊ ምዕራፍ ወቅት በግድብ ዙሪያ በአንድነት በመቆም የራሳቸውን አስተዋጽ እንዲያበርክቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ተሳታፊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በበኩላቸው ለተመቻቸው የውይይት መድረክ ያላቸውን ምስጋና ገልጸው፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግድብ ሁሉንም የሚመለከት የጋራ አጀንዳ መሆኑን አንስተዋል። የውስጥ አንድነት በማጠናከር የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚደረገው የተለያየ ጫና ለመቋቋም ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙና ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል። የፓርቲዎቹ አመራሮች ተመመሳሳይ መድረኮች መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *