በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ለአገራችን ሰላም፣ልማትና አንድነት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አስታወቁ።

በዋሽንግተን የኢፌዲሪ ኤምባሲ የ2016 ዓም የዘመን መለወጫ ዋዜማ በዓልን በዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ከሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በድምቀት አክብሯል።
በአሜሪካ የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ስለሺ በቀለ ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱ ዓመት ካሳለፍናቸው ስኬቶችና ፈተናዎች ትምህርት በመቅሰም ለአገር የሚበጁትን እንደ ወረት ይዘን ለአገራችን ልማትና አንድነት ቃል የምንገባበት ወቅት ነው ብለዋል።
መጪውን አመት ከዛሬዋ ዋዜማ ቀን ጀምረን በአንድነት፣ በመተዛዘን፣ በመቻቻል፣ እና በመከባበር በአብሮነት ለጋራ ድል በአዲስ ልብና በአዲስ መንፈስ መነሳት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው አመት በአገራችን በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸዉን ከእነዚህ መካከል ለአብነት የሚጠቀሰዉ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጦርነት ቆሞ በድርድር መፍታት መቻሉ ፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የዉሃ ሙሌት በድል መጠናቀቁ ፣ ኢትዮጵያ ወደ ብሪክስ አባል ሀገራት መቀላቀልዋ ፣ ሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስኬቶች መገኘታቸዉ እና በአንጻሩም በአሁኑ ወቅት በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች እንዲፈቱ ትኩረት አግኝተዉ እየተሰራባቸዉ እንዳለ አዉስተዉ ይህም ለቀጣይ ስኬቶቻችን ስንቅ እንደሚሆን ጠቁመዋል ።
አገራችን በገጠሟት ፈተናዎች ሁሉ ዳያስፖራው እውቀቱን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን ጭምር ሳይሰስት ላበረከተው አስተዋጽኦ ምስጋና ያቀረቡት አምባሳደር ስለሺ፤ አሁንም ወደማይናወጽ ሰላም፣ ልማትና አንድነት ለመሻገር ዳያስፖራው ገንቢ ሚናውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተሳተፉ የሀይማኖት አባቶችም አዲሱ ዓመት ሰላም የሰፈነበት፣ ዜጎች ተረጋግተው የሚኖሩበት እና አብሮነት የሚጎለብትበት እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የዳያስፖራ አደረጃጃት ተወካዮችና ታዳሚዎች በበኩላቸው በአገራችን የሚታዩ የሰላም መደፍረሶችን በዘላቂነት ለመፍታት ሁሉም አካል ለንግግር ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን ለአገራቸው የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በአዲሱ ዓመትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *