ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን የምታስተዳድርበት መንገድ ከውጭ ሊነገራት አይገባም፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (May 25, 2021)
ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን የምታስተዳድርበት መንገድ ከውጭ ሊነገራት እንደማይገባ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ በአገሪቱ አመራሮች ላይ የጉዞ እገዳ ለመጣል መወሰኗን ተከትሎ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አገራዊ መግባባት እንዲፈጠር ከሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲሰራ የቆየው ከውጭ ስለተገፋ ሳይሆን በአገር ውስጥ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ለማድረግ ትክክለኛ መንገድ ሆኖ ስላገኘው መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
መንግስት በኢትዮጵያ ፓርላማ ሽብርተኛ ሆኖ ከተፈረጀው የሕወሓት ቡድን ጋር እንደማይደራደር ሊሰመርበት ይገባል ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ግልጽ እንዳደረገው ሁሉ፣ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚያደርገው ጥረት ተገቢ አይደለም ብቻ ሳይሆን ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይዋን የምታስተዳድርበት መንገድ ከውጭ ሊነገራት እንደማይገባም ተገልጿል፡፡
በትግራይ ክልል የተፈጸመው የሰብአዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግስት በተግባሩ የተሳተፉትን አካላት ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራ መሆኑ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሲያደርግ የነበረውን የምርመራ ውጤት እና ተጠያቂነት እና ፍትሕ እንዲሰፍን የወሰዳቸውን እርምጃዎች ይፋ ማድረጉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የጋራ ገለልተኛ ምርመራ ሥራ መጀመራቸውም የተገለጸ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ መንግስት ጋባዥነት የአፍሪካ የሰብአዊ እና የህዝቦች መብት ጥበቃ ኮሚሽንም ምርመራ እያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በትግራይ ክልል ለተከሰተው ሰብአዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ለመስራት ቁርጠኝነቱን መግለጹ ብቻ ሳይሆን፣ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪዎች በትግራይ ክልል ውስጥ ያልተገደበ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ መፍቀዱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ያለውን ውስን ሀብት እና ከአጋር አካላት የተገኘውን ዕርዳታ በመጠቀም በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዲደርስ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ እየሰጡ ያሉ አካላት እያጋጠመ ያለው ችግር የአቅም እና የተጨማሪ ዕርዳታ ፍላጎት እንጂ የተደራሽነት ችግር እንዳልሆነ ይገነዘባሉ ብሏል ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፣ የአሜሪካ መንግስትን ጨምሮ ከሌሎች ዓለም አቀፍ አጋር አካላት ጋር በትብብር በመስራት ውጤት በማስመዝገብ ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ የአሜሪካ መንግስት ለመጣል የወሰነው የጉዞ እገዳ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ከመጉዳቱም በላይ የተመዘገቡ ውጤቶችን የሚጎዳ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ይህ የሁለቱ አገራት የቆየ ወዳጅነት ላይ ችግር የሚፈጥር ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካ መንግስት ጋር የሚያደርገውን ግንኙነቶች እንደገና ለማጤን የሚገደድ መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው፣ ይህ ደግሞ ከሁለትዮሽ ግንኙነትም ባለፈ ሌላ አንድምታ ይኖረዋል ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ያሉትን ችግሮች ለመፍታት እና በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም እና ብልጽግና ለመምጣት የሚያደርገው ጥረት በዚህ የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ ወደኋላ የማይመለስ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ አላስፈላጊ ጫና ማሳደሯን ለመቀጠል መወሰኗን በመስማቱ ማዘኑን መንግሥት ገልጿል፡፡
ቀደም ሲልም አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጠው የነበረውን ኢኮኖሚያዊ እና የፀጥታ ድጋፍ ለመቀነስ መወሰኗን መግለጫው አስታውሷል፡፡
ውሳኔው ኢትዮጵያ የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሜሪካ መንግሥት አስተዳደር ጋር ገንቢ የሆነ ትብብር እያደረገች ባለችበት ወቅት የተላለፈ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ ለስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ደርሰው የተመለሱትን አዲሱን የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሚስተር ጄፍሪ ፌልትማንንም የተቀበለችው በዚሁ መንፈስ እንደነበርም ጠቅሷል፡፡
መልዕክተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከአገሪቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ተገናኝተው መምከራቸውንም አስታውሷል፡፡
ውሳኔው ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል ብላ ተስፋ የጣለችበትን ሀገር አቀፍ ምርጫዋን ለማድረግ እየተዘጋጀች ባለችበት ሰዓት የተላለፈ መሆኑም የተዛባ ትርጉም ያሰጠዋል ብሏል መግለጫው፡፡
6ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ የመንግሥት አስተዳደርን ከመቀየር በተጨማሪ አካታች ለሆነ ምክክር በር ይከፍታል ተብሎ እንደሚጠበቅ መግለጫው ጠቁሟል፡፡
እናም በዚህ ወሳኝ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካ አቻው ይጠብቅ የነበረው ድጋፍን እንጂ እንዲህ ያሉ በሀገራዊ ምርጫው ላይ ጥላ የሚያጠሉ የተዛቡ እርምጃዎችን አይደለም ብሏል መግለጫው፡፡
ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ላላት የቆየ ወዳጅነት ትልቅ ግምት እና ቦታ እንደምትሰጥ የጠቀሰው መግለጫው የጉዞ እገዳውን ጨምሮ በአሜሪካ መንግስት ሊወሰዱ የታሰቡት እርምጃዎች በሁለቱ አገራት መካከል የቆየውን ታሪካዊ ግንኙነት ክፉኛ እንዳይጎዱት መንግሥት ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡
የአሜሪካ መንግስት አስተዳደር የኢትዮጵያ መንግስትን ከሁለት ሳምንታት በፊት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀው ሕወሓት ጋር በተነፃፃሪነት ለማቅረብ ያሳየውን አዝማሚያም “አሳዛኝ እና የአስተዳደሩን የተዛባ አካሄድ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ” ሲል መግለጫው ተችቷል፡፡
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!