የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በሜኔሶታ ከክልሉ ተወላጆች ጋር ውይይት አደረጉ

እ.ኤ.አ. ሜይ 3 ቀን 2025 የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡመድ በአሜሪካ ሜኔሶታ ግዛት ነዋሪ ከሆኑ የክልሉ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ጋር በክልሉ እየተካሄደ ባለው የልማት ስራዎች እና ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አደረጉ።

ርዕሰ መስተዳድሯ በክልሉ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና እየተካሄደ ስላለው የልማት እንቅስቃሴ እንዲሁም ከዳያስፖራው ምን እንደሚጠበቅ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በክልሉ ያለው የሰላም ሁኔታ በእጅጉ የተሻለ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ የተሻለ ሁኔታም የክልሉን ልማት ለማፋጠን እና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ መሰረት እንደሆነ ተናግረዋል። ከዚህ አንጻር ዳያስፖራው በክልሉ እየተካሄደ ያለውን ልማት መደገፍ እንደሚገባው እና በኢንቨስትመንትም መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዱአለም በተወካያቸው አቶ ተራመድ አዳነ አማካኝነት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ስለክልላቸው ብሎም ስለሀገራቸው ትክክለኛ መረጃዎችን በማግኘት እየተካሄደ ባለው የልማት እንቅስቃሴ ላይ የራሳቸውን አሻራ ለማሳረፍ እንዲህ አይነት መድረክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቅሰው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግንባታ ከ98 በመቶ በላይ መጠናቀቁን፤ በዚህም ሂደት በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልድ ኢትዮጵያውያን ያደረጉት ተሳትፎ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነው ካሉ በኋላ በዚህ ረገድ የጋምቤላ ኮሚኒቲ አደረጃጀት ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበረ በመጥቀስ በቀጣይ ግድቡ ተጠናቆ ሪቫን እስክንቆርጥ ድረስ የሚቻላቸውን ሁሉ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በውይይቱ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በቂ ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ዳያስፖራው በክልሉ ለተጀመሩ የልማት ስራዎች ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *