98ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች (June 22, 2021)
ሰኔ 15 ቀን 2013 ዓ.ም፣
አዲስ አበባ ፣
98ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች (June 22, 2021)
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 98ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡
1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የአፍሪካ አመራር ልህቀት አካዳሚ ለማቋቋም በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ሲሆን የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ሁለንተናዊ ሰላም፣ ዲሞክራሲና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና ካላቸው ወሳኝ አካላት አንዱ አስተማማኝ አቅም ያለው አመራር መኖር በመሆኑ ተከታታይና ሁሉን አቀፍ የአመራር ልማት ማካሄድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ በንድፈ ሀሳብ የተደገፈ ተግባር ተኮር የአመራር ስልጠና እና የማማከር አገልግሎት በመስጠት ብሎም ችግር ፈቺ ምርምር በማካሄድ ሳይንሳዊ የለውጥ ሀሳቦችን በማመንጨት በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ሁለንተናዊ ብልጽግና እና መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ የሚተጋ የአመራር ልህቀት ማእከል ማቋቋም የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ መብትና ግዴታዎች ለማእከሉ የሚተላለፉ ይሆናል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ረቂቅ ደንብ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ ግብዓቶችን በማከል በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው በብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ረቂቅ ስትራቴጂ ሰነድ ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለህዝቦቿ ተጠቃሚነት የላቀ አቅም መፍጠር የሚያስችል ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማካሄድ ላይ ትገኛለች፡፡ ይህ ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂም የዚሁ ለውጥ ጉዞ ዋነኛ አካል ነው፡፡ ስትራቴጂው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የክፍያ ስነ ምህዳሩን በማዘመን ውስን የጥሬ ገንዘብ እንቅስቃሴ ያለውና የፋይናንስ አካታችነቱ የጎለበተ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ፍኖተ ካርታ በመሆን ያገለግላል፡፡ በተጨማሪም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ዲጂታል አሰራር በማሸጋገር የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ፣ የስራ እድል ለመፍጠር፣ የሴቶችን የኢኮኖሚ ተሳትፎ ለማሳደግ ከሚካሄዱ ሀገር በቀል የሪፎርም ተግባራት ጋር በቅንጅት የሚፈጸመው ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ ኢትዮጵያ ያስቀመጠችውን አካታች የኢኮኖሚ እድገት፣ የላቀ ብልጽግና እንዲሁም የተሻለ የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ግብ ለማሳካት የሚያግዝ በብሔራዊ ዲጂታል ክፍያ ረቂቅ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ ምክር ቤቱም በረቂቅ ስትራቴጂ ሰነዱ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶች በማከል በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
3. ምክር ቤቱ በመጨረሻ የተመለከተው የኢትዮጵያ መንግስት ከፈረንሳይ እና ከጣልያን መንግስታት ጋር ያደረጋቸውን የመከላከያ ትብብር የሁለትዮሽ ስምምነቶች ነው፡፡ የሁለትዮሽ ስምምነቶቹ በኢትዮጵያ እና በሃገራቱ መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያጠናክሩ እና ጸንቶ የቆየውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ለማጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቶቹ በመከላከያ ዘርፍ ትብብር ለማድረግ ከማስቻላቸውም በላይ የአገራችንን የመከላከያ ሰራዊት ወታደራዊ የቴክኒክ አቅም እና ክህሎት ለማጎልበት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው የታመነባቸው የሁለትዮሽ ስምምነቶች በማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ተደግፈው ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱ በረቂቅ የስምምነቶቹ ላይ ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል ይጸድቁ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፉ ወስኗል፡፡
//
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!